”ትዕግስት” የምንለውን የዳቦ ስም ስፍራ እንፈልግለት

(በዲን አባይነህ ካሴ)

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ኃይሌ ጋርመንት የሚባለው ሰፈር ባገኙት ክፍት ቦታ ላይ በአንድ ቀን አጥረው በአንድ ቀን መስጊድ ሲገነቡ ፖሊስ ስንኳን ሊቆጣ ሥራቸው እንዳይታጎል ሲጠብቃቸው ነበር።

አምቦ ከተማ ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩን አናሳልፍም ብሎ መንገድ በዘጋው ወጣት ፊት መሣርያውን ዘቅዝቆ እጁን ዘርግቶ ሲለምንም ዐይተናል።

መስጊድ በግንባታ ሰበብ ፈረሰ ሲባል በአንዲት መስመር የፌስ ቡክ ትእዛዝ ምትክ ብቻ ሳይኾን በርከትከት ያለ ሰፊ መሬት እነሆኝ ሲሉ ታዝበናል።

ቤተ ክርስቲያን ላይ ሲኾን ግን እነዚህ ባሕርያቱ ይለዩታል። ሀገር ጥሶ በገባ ጠላት ፊት እንደሚፋለም ወታደር የመጨረሻውን ጭካኔውን አሟጥጦ ይጠቀማል።

– [ ] ሰላማዊ ሰልፍ ሲባል በመቃብራችን ላይ ይላል
– [ ] በቅዱሳት የዐደባባይ በዓላት ላይ ቤተ ክርስቲያን ምልክቶቿን እንዳትጠቀም እንቅልፍ አጥቶ ይውረገረጋል።
– [ ] ምእመናን በሀገራቸው ሰንደቅ አሸብርቀው መታየታቸው ጋኔኑን ያስነሣበታል። ልብስ አስወልቄ ራቁት ካላስሔድሁ ብሎ ይዋደቃል።
– [ ] ምእመናን ረዘም ላለ ጊዜ ሲንከባከቡት የነበረን ቦታ ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ሲጠቀሙበት ዛሩ እያወረደ ይፈጨዋል። በውድቅት ሌሊት እንደሚለቀቁ አጋንንት በምስኪን አማኞች ላይ ጥይት በሩምታ ይተኩሳል። የሰውን ሕይወት እንደ ቅጠል ያረግፋል።

ለሙስሊሞች በተደረገላቸው ቅናት የለንም። ለአድልዎው ግን ግልጽ ማሳያ ስለኾነ መጠቀሱ ማንንም ሊያስከፋ አይገባም። ለምን ተደርጎላቸው? ሳይኾን ለእኛ ጊዜ ሌላ ለምን ይደረጋል ነው ጥያቄው?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደሌሎች ቤተ አምልኮ ፈረሰብን ብለን ልናቆም አልቻልንም። አያይዘን ከካህን እስከ ምእመን ይህን ያኽል ተገደለም እንላለን እንጅ። ሞታችን ሁሉ አጃቢ አለው። የአካል ጉዳት፣ የንብረት ማጣት (በቃጠሎ እና ዝርፊያ)፣ ታስሮ መንገላታት፣ ዛቻ እና ማስፈራራት እስከ ማፈናቀል። ቤተ ክርስቲያን በሌሊት ሽምቅ ጥቃት የሚደርስባት የመጨረሻ ጠላት ኾና መፈረጇን ያሳያል። ሌሊት ጦር የሚዘምተው ጥቃትም የሚሰነዘረው በአደገኛ እና በከባድ ጠላት ላይ ነው።

ይህንን ዝም ማለት ትዕግስት የሚባል የዳቦ ስም ሲሰጠው ደግሞ የበለጠ ሕማሙ እጥፍ ድርብ ይኾናል። ቆፍጣናውን ኦርቶዶክሳዊ በምዕራባዊ የተልፈሰፈሰ ስብከት ከደርዙ አስወጣነውና ለትልቁም ለትንሹም አልቃሻ አደረግነው።

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም መልክ ያለው አስተምህሮ አላት። ልኬቷ አይዛነፍም። ፈተና እና መከራን አንድ አድርጎ የሚጨፈልቅ ባህልም (thought) የላትም። ያ ባይኾን ዘመነ ሰማዕታትን ባልተሻገረችው ነበር። በሮም ኢምፓየር የክርስቲያን መከራ የቆመው አላውያንን ማስቆም ሲቻል ነው።

ለቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ትእምርተ መስቀል ሲሰጠው በፈረሱ ጆሮ በጦሩ ጉሮሮ እያደረገ መምለኪያነ ጣዖታቱን ድል አድርጎ ክርስትና ከመሰደድ ነፃ ወጣ። ትዕግስት ደርዝ አለው። የምንታገሳቸው ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ሁሉ የማንታገሳቸውም መከራዎች አሉ። ሳንደበላልቅ ኹለቱንም በተዐቅቦ ይዘን መገኘት ይኖርብናል።

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን በቤተ ምኩራብ ያየውን ጥዩፍ ሥራ በኃይል ያራቀው ትዕግስት ተለይቶት ነው እንበልን? እንዲያ ብንል የባሕርይ ገንዘቡን መቀማት ይኾንብናል። ነገር ግን ለሁሉም ልክ አለው ሲለን ነው። የምንታገስበት ጊዜ አለ የማንታገስበት ጊዜ አለ።

ሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ንጉሥ ዑልያኖስን ያስወገደው ትዕግስት ስላልነበረው ነበርን? ቅዱስ ቴዎድሮስ በናልድዮስ ንጉሠ ቁዝን በጦሩ ጉሮሮ የቀሰፈው ትዕግስት አጥቶ ነበርን?

ልክ የሌለው እንጉርጉሮ ትዕግስት በተባለ የዳቦ ስም ምክንያት እያሰሙ መኖር ክርስቲያናዊ ሕይወት አይደለም። ስለዚህ:-

– [ ] በሕግ የሚጠየቀውን በሕግ
– [ ] በኃይል የሚመጣውን በኃይል

ለመመከት መደራጀታችንን እንቀጥል። ባንደራጅ ኖሮ ሊመጣ የነበረው ጥፋት ከባድ ነበረ። ብዙ የጥፋት ዕቅድ እንደ ጥቁር ደመና ከብዶ ሊወርድብን ነበረ። በአበው ጸሎት በመሰባሰባችን ምክንያት ኃያሉ እግዚአብሔር ሳይደርስ አቅልጦ ያስቀረው ብዙ ነው።

ጥቃቅን መደለያዎች ወደቤት እንዳያስገቡን ደጋግመን እናስብ። በምክትል ከንቲባው መግለጫ ለሕይወት መጥፋት ምክንያት በኾኑት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንወስዳለን መባሉ ሊያዘናጋን አይገባም።

– [ ] መጀመሪያ ማን ለምን ቢልካቸው ነው እንደዚያ ሰው በላ የኾኑት?
– [ ] ወደፊት ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይገጥምስ ምን መተማመኛ መንግሥታቸው ይሰጣል?
– [ ] መቃኞው ፈርሶ ነው የሚቀረው? ቦታው ይከበራል ወይስ አይከበርም?
– [ ] በታጠቁ የመንግሥት ሠራዊት ሕይወታቸውን ላጡት ካሣ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸውም ካሣ ታስረው በእንግልት ላሉ ወንድሞቻችን መፈታትን ይሰጣልን?
የሚሉት ጥያቄዎች በቅድሚያ መመለስ አለባቸው።

#ጴጥሮሳዊው_ሕብረት እያደረገ ላለው መነሣሣት ድጋፍ ይፈልጋል። አገልግሎቱም ከፍ ማለት ይጠበቅበታል።

የወንድሞቻችንን የሚሊዮን ድንበሩን እና የሚካኤ ፋኖስን ነፍስ ሀገረ ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን! በሰማዕታቱ ዕቅፍ ያኑርልን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.